ዜግነት ላይ ያተኮረ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ሊመሰረት ነው


አዲሱን ፓርቲ ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ሰማያዊ ፓርቲ ሲሆን ትናንት ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ራሱን አክስሟል።
ይህን ያደረገው ራሱን አብነት ለማድረግ መሆኑን የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ተናግረዋል።
አቶ የሽዋስ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቅላላ ጉባኤው ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ከራስ ይልቅ ለሀገር ቅድሚያ በመቆም ነው ብለዋል።
የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አባል አቶ አንዷለም አራጌ የሰማያዊ ፓርቲ ውሳኔ የሚደነቅ መሆኑን ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ሌሎች ፓርቲዎች እና ንቅናቄዎች ይህን ፈለግ ተከትለው የውህደቱ አካል ለመሆን ተስማምተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አቶ የሽዋስ አንስተዋል።
በውህደት ሊፈጠር የታሰበው አዲሱ ፓርቲም የኢትዮጵያ አንድነት፣ የዜጎች ነጻነት፣ የመሬት ባለቤትነት እና የህዝቡ የስልጣን ባለቤትነትን መሰረቱ ማድረጉንም አስረድተዋል።
አቶ አንዷለም በበኩላቸው ሊፈጠር የታሰበው የአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ተመሳሳይ አላማ ባነገቡ ፖለቲከኞች እና ፓርቲዎች መጀመሩን ጠቅሰው፥ የፓርቲው አሰላለፍ ውህደት መሆኑን አውስተዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ ደግሞ በዜግነት ላይ ያተኮረ ፓርቲ መመስረት ብቻ ሳይሆን በብሄር ላይ የተመሰረተ ፓርቲ እንዳይቋቋምና እንዳይፈቀድ እንታገላለን ብለዋል።
አቶ አንዷለም ኢትዮጵያ ሰው በዜግነት ተወዳድሮ ሀሳቡን ሽጦ የሚኖርባት ሀገር እንድትሆን እና ይህን ሃሳብ ለህዝቡ የማስረዳት ሃላፊነት እንዳለባቸው አንስተው፥ ህዝቡ ግን በሂደቱ ዋናው ገዥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ውህዱ ፓርቲ መነሻውን ከታች በማድረግ አደረጃጀቱ ከመሰረቱ ተጠናክሮ እንዲመጣ የሚያደርግ አካሄድ እየተከተለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የፊታችን መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ይቋቋማል የተባለው ፓርቲ አሁን ላይ አብረው የሚሄዱትን የመለየት ስራ እየሰራ ሲሆን፥ በቀጣይ በየወረዳው የማስመረጥ ሂደት ይኖራል ተብሏል።



ምንጭ፡-ኤፍ ቢ ሲ ታህሳስ 23 /2011
 

Comments

Popular posts from this blog

ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቦች የልምምድ እና ስቴዲየም መስሪያ ቦታ ሊሰጥ ነው

Baruu barsiisun akka hin gufanne hawaasni tumsa taasisuu qaba- Dr Tolaa Bariisoo