በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ አጋማሽ መርሃ ግብር ዛሬ ሶስት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ከቀትር በኋላ የማርኮ ሲልቫው ኤቨርተን ከሌሲስተር ሲቲ 9 ሰዓት ከ 30 ላይ ይጫወታል። በሶስት ጨዋታዎች 2 ተሸንፈው አንድ ያሸነፉት ኤቨርተኖች የአዲሱን አመት የመጀመሪያ ጨዋታ ጉዲሰን ፓርክ ላይ ያደርጋሉ። ማምሻውን 12 ሰዓት ላይ ደግሞ አርሰናል የምዕራብ ለንደኑን ፉልሃምን ኢሚሬትስ ላይ ያስተናግዳል። አርሰናል በሳምንቱ መጨረሻ በሊቨርፑል ከደረሰበት የ5 ለ 1 ሽንፈት በኋላ፥ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ካለው ፉልሃም ጋር የሚያደርገው የምሽት ጨዋታ ይጠበቃል። ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ደግሞ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ወደ ዌልስ አቅንቶ ከካርዲፍ ሲቲ ጋር ይጫወታል። የለንደኑ ክለብ በ20ኛው ሳምንት መርሃ ግብር በሜዳው በወልቭስ ያልተጠበቀ የ3 ለ 1 ሽንፈት ማስተናገዱ ይታወሳል። ፕሪሚየር ሊጉ ነገም ሲቀጥል ስድስት ጨዋታዎች ምሽት 4 ከ 45 ላይ ይደረጋሉ፤ ከነገ በስቲያ ደግሞ ማንቼስተር ሲቲ ከሊቨርፑል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። ሊጉን ሊቨርፑል በ54 ነጥብ ሲመራ፥ ማንቼስተር ሲቲ በ47፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ45 እንዲሁም ቼልሲ በ43 ነጥብ ይከተሉታል። ሃድስፊልድ፣ ፉልሃም እና በርንሌይ ደግሞ በደረጃው ግርጌ ላይ ይገኛሉ። ፕሪሚየር ሊጉ በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ ሁለተኛ አጋማሽ መርሃ ግብሩን የሚጀምር ሲሆን፥ በመሃል የኤፍ ኤ ካፕ 3ኛ ዙር ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 23 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ)